ዛሬ ጠ/ሚ አብይ አህመድ በባህር ዳር ንግግራቸው የዳንኤል ክብረትን ፅሁፍ ጠቅሰው ተናግረው ነበር
ሙሉ ፅሁፉ እነሆ
ጫካው ለዛፎች ብቻ
October 13, 2011 at 1:12am
በአንድ ወቅት በጫካ ውስጥ ያሉ ዛፎች እንዲህ ሲሉ መከሩ፡፡

«እነዚህ አራዊት እኛ ጋ ለመጠለል ይመጣሉ፡፡ እኔ የእነርሱን ማንኮራፋት መስማት ሰልችቶኛል» አለ የዝግባ ዛፍ፡፡

«እኔ ደግሞ ከሁሉም የሰለቸኝ እኔ ላይ ወጥተው ሲራኮቱ እየቀነቁኝ ነው» ጽድ መለሰ፡፡

የሶደሬኦንድማንድን አፕልኬሽን በማውረድ ፊልሞች ከመለቀቃቸው በፊት ተመልከቱ Download SodereOnDemand app watch full movies before they are released. Apple, Android and Roku SodereOnDemand apps. 

          

«ከሁሉም የሚብሰው የእኔ ነው» አለ ግራር፡፡ «ከሥሬ ይመጡና ኩሳቸውን ይጥላሉ፡፡ እኔ ሽታውን መቋቋም አቅቶኛል»

«አንዳንዶቹማ»አለ ዋርካ «ከኔ ሥር መጥተው ጉድጓድ ቆፍረው ይኖራሉ» ሁሉም ምሬታቸውን አወሩ፡፡

«ይህንን ያህል ካስመረሩን ለምን ዝም እንላቸዋለን? ድራሻቸውን ማጥፋት ነው» ዝግባ እየተንጎማለለ ፎከረ፡፡

«ልክ ነው የአንበሳ እና የነብር መራኮቻ መሆናችን ሊያበቃ ይገባል» ጽድ ግራ ቅርንጫፉን አንሥቶ ደገፈ፡፡

«ከዛሬ ጀምሮ አንድም አንበሳ እና ነብር እዚህ አካባቢ እንዳይደርስ መደረግ አለበት» ዋርካ በጎርናና ድምፁ አናወጠው፡፡

ከዚያም «ጫካው ለዛፎች ብቻ» የሚል መፈክር ቅርንጫፎቻቸው ላይ ሰቀሉ፡፡

«ይህንን ቦታ ጫካ እንዲሆን ያደረግነው እኛ ዛፎች ነን፡፡ በብርድ እና በፀሐይ እየተንገበገብን የታገልነው እኛ ነን፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ስንት መከራ አይተናል፡፡ እኛ በመሠረትነው ጫካ ማንም ሊጠቀም አይችልም፤ ጫካው ለዛፎች ብቻ» ይላል ከመፈክሩ ሥር የተፃፈው ማብራርያ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ወይራ ዝም እንዳለ ነው፡፡

«ምነው አንተ ያንን ክርፋታም ሽታ ወደኽዋል መሰል» አሉት በሽሙጥ፡፡

«እኔም እንደ እናንተ በአራዊቱ መኖር ችግር አለብኝ፡፡ ሽታውም፣ ጩኸቱም፣ መወዝወዙም፣ መሰበሩ መርሮኛል፤ ግን ደግሞ እነርሱ አራዊት ናቸው፡፡ ከዚህ ጠባያቸው ውጭ መሆን አይችሉም፡፡ ዛፍ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በችግሩ ላይ እስማማለሁ፤ በመፍትሔያችሁ ላይ ግን አልስማማም» አለ ወይራ፡፡

ሁሉም እየተመናቀሩ ከበቡት፡፡

«እና የማንም አውሬ መጨዋቻ እንሁን ነው የምትለው?» ዋርካ ጮኸበት፡፡

«እስኪ ንገረኝ አንበሳ እና ነብር መጡ፣ ቀሩ ምን ይጎድልብናል?» ግራር አፋጠጠቺው፡፡ «በዚች ምድር አንዱ ያለ ሌላው ሊኖር አይችልም፡፡ ልዩነቱ ያኛው የሚሰጠንን ጥቅም ልናውቀው ወይንም ላናውቀው መቻላችን ነው፡፡ ምንጊዜም የዚያኛውን ወገን ችግሩን ብቻ የምናየው ከሆነ ጥቅሙን የምናይበት ዓይን አይኖረንም፡፡ ቢያንስ እነርሱ የሚጥሉት ነገር ቢሸተንም አፈሩን ያዳብርልናል፤ ለኛም ምግብ ይሆነናል፡፡ ለምን ችግሩን ብቻ ታያላችሁ፡፡ እኛ መጠለያ እንሰጣለን፣ እነርሱ ደግሞ ምግብ ይሰጣሉ፤ ሌላም ዛሬ ያላወቅነው ነገር ያደርጉልንም ይሆናል፡፡ ተባብረን እንኖራለን፡፡ ሳይደጋገፉ መጥፋት ይቻላል፤ ሳይደጋገፉ መኖር ግን አይቻልም»

አንድ ጊዜ ሁሉም እንደ ብራቅ ጮኹበት፡፡

«የእነርሱ ማዳበርያ ጥንቅር ብሎ ይቅር፡፡» አለ ዝግባ፡፡ ሁሉም አጨበጨቡ፡፡

«እኔ ወስኛለሁ አንድ ነብር አንድ አንበሳ እዚህ ቢመጣ የማደርገውን ዐውቃለሁ፤ ጫካው ለዛፎች ብቻ» ዋርካ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ሌሎቹም አንገታቸውን እየነቀነቁ «ጫካው ለዛፎች ብቻ» እያሉ ፈክረው ተመለሱ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነብር መጣ፡፡ ዋርካው ላይም ወጣ፡፡ ያን ጊዜ የዋርካው ቅርንጫፎች እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ተርገፈገፉ፡፡ የሌሎቹ ዛፎች ቅርንጫፎችም እየተወራጩ ነብሩን በጥፊ ይመቱት ጀመር፡፡ በሁኔታው የተደናገጠው ነብር እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈረጠጠ፡፡ ፈርጥጦም አልቀረ ወገኖቹን ሰበሰበና «እዚህ ጫካ ውስጥ አንዳች መዓት ወርዷል፤ «ጫካው ለዛፎች ብቻ» የሚል መፈክርም አይቻለሁ፡፡» እያለ ያጋጠመውን ነገር ነገራቸው፡፡ ከዚያም ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የነብር ዘር ጫካውን ጥለው ጠፉ፡፡

በማግሥቱ አንበሳ ከነደቦሎቿ መጣች፡፡ ከዝግባው ዛፍ ሥርም አረፈች፡፡ የዝግባው ዛፍ ሥሮቹን አወጣና ደበደባት፡፡ ሌሎቹ ዛፎችም ቅርንጫፎቻቸውን እያስጎነበሱ የማርያም ጠላት ብለው ጨፈጨፏት፡፡ አንበሲቷ አይታው የማታውቀው ነገር ስለገጠማት ደቦሎቿን ሰብስባ ሸሸች፡፡ ከዚያ በኋላም በጫካው ውስጥ አንበሳ አልታየም፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ አራዊቱን ሁሉ ገርፈው እና አስደንግጠው አባረሯቸው፡፡

ቀናት፣ ሳምንታት እና ወራት አለፉ፡፡ አንድም አውሬ ብቅ ሊል አልቻለም፡፡ ዛፎቹ ከሽታው ተገላገሉ፡፡ በላያቸው የሚዘል በሥራቸው የሚጠለል አውሬ የለም፡፡ ሁሉም የጀግንነታቸውን ውጤት በኩራት ይተርኩ ጀመር፡፡ እንዳሉትም ጫካው ለዛፎች ብቻ ሆነ፡፡ የሚያገሣ አንበሳ፣ የሚጮኽ ጅብ፣ የሚያስገመግም ነብር አልነበረም፡፡

ወይራ ግን በነገሩ ሁሉ አዘነ፡፡

አንድ ቀን አራት ሰዎች የሆነ ነገር ተሸክመው ወደ ጫካው መጡ፡፡ በቁመቱ ዘለግ ያለው ዝግባ በሩቁ ሲመለከታቸው ሊያውቃቸው አልቻለም፡፡ «አራት ሰዎች የሆነ ነገር ይዘው ወደ ጫካችን እየገቡ ነው» አለና አሰምቶ ጮኸ፡፡ ጽድ መጡ ወደተባለበት ሲዞር እውነትም አራት ሰዎች የሆነ ነገር ይዘው ገቡ፡፡

«የያዙት ምንድን ነው?» ሁሉም ጽድን ጠየቁት፡፡ ነገር ግን በዚያ ጫካ ውስጥ አደን ለማደን የሚመጡ ሰዎች ከሚይዙት መሣርያ በቀር ሌላ መሣርያ ታይቶ አይታወቅምና ሊያውቁት አልቻሉም፡፡

ወይራ አሾልኮ ተመለከታቸው፡፡ ዐወቃቸውም፡፡ «የፈራሁት ይሄንን ነበር» አለ በኀዘን ድምጽ፡፡ ሁሉም ወደ እርሱ ዞሩ፡፡ «እነዚህ ሰዎች ዛፍ ቆራጮች ናቸው» አለ በቅርንጫፉ መሬቱን እየደበደበ፡፡

«እንዴት ሊመጡ ቻሉ?» አለ ዋርካ ፍርሃት እያራደው፡፡

«አያችሁ አራዊቱን አባራችሁ ዛፍ ቆራጮችን አመጣችሁብን፤ ለጊዜያዊ ሰላም ስትሉ ዘላቂ ሰላማችንን ነጠቃችሁን» አለ ወይራ፡፡

«የእነርሱን መምጣት እንዴት ከአራዊቱ መሄድ ጋር ታያይዘዋለህ፣ ምን ያገናኘዋል?» ጽድ አፈጠጠ፡፡

«እዚህ ጫካ ውስጥ አንበሳ፣ ነብር፣ ጅብ፣ ተኩላ፣ ቀበሮ ሌሎችም ነበሩ፡፡ ሰው ደግሞ አንበሳ እና ነብር ይፈራል፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው

ዛፍ ለመቁረጥ የሚመጣ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ጥቂቷን ሽታ መቋቋም አቅቶን አንበሳውን እና ነብሩን አባረርናቸው፡፡ አላወቅንም እንጂ እነርሱ ለኛ ጠባቂዎቻችን ነበሩ፡፡ የተከበርነው በእነርሱ ነበር፡፡ ጫካው ባዶ ሲሆን ዛፍ ቆራጮች መጡ» አለ ወይራ፡፡

«አሁን ምን ይሻላል?» ዋርካ ዕንባ ዕንባ አለው፡፡

«በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ

አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ

ይላሉ ሰዎች ሲተርቱ፡፡ አሁንማ ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ዓለም አንዱ ያለ ሌላው ርዳታ መኖር አይችልም፡፡ ሁላችንም የሌላው ጥገኞች ነን፡፡ የማንፈልገው እንጂ የማያስፈልገን ነገር የለም፡፡ የማናደንቀው እንጂ የማይጠቅመን የለም፡፡ የኛ ህልውና ለብቻው ሊጠበቅ አይችልም፡፡ የኛ ህልውና ከሌሎች ህልውና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኛ ሰላም ብቻውን ሊጠበቅ አይችልም፤ የኛ ሰላም ከሌሎች ሰላም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን በሌሎች ላይ የደረሰውን የምንረዳው ሲደርስብን ብቻ ነው፡፡ ያ ደግሞ ምንም ማድረግ የማይቻልበት ሰዓት ነው፡፡ ሌሎችን እንደሚያስፈልጉን ከተረዳን፣ ለሌሎች መብት እና ጥቅም መቆም አለብን፤ ሌሎቹም እንደኛው እንዲኖሩ መፍቀድ አለብን፤ መፍቀድ ብቻም አይደለም ለእነርሱ መኖር እኛ አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን፡፡

«ዕንቁራሪት ያለቺውን ታውቃላችሁ?» ጠየቀ ወይራ

«እስኪ ከመቆረጣችን በፊት ንገረን» አሉት፡፡

«እርሷ ኩሬ ውስጥ ሆና እያለ እዚያ ማዶ ቤት ይቃጠላል አሉ፡፡ እሳቱን እያየች ትጨነቃለች፡፡ እንዳጋጣሚ አንድ ሰው በአጠገቧ ሲያልፍ ወዳጄ «ለፖሊስ ልትደውልልኝ ትችላለህ?» ትለዋለች፡፡ ሰውዬውም ገርሞት «ምን ሆንሽ ብዬ ነው የምደውልልሽ» ይላታል፡፡ «ኧረ እባክህ እዚያ ማዶ እሳት ተነሥቷል ብለህ ደውል» አለቺው፡፡ ሰውዬውም «እሳቱ ያለው እዚያ ማዶ አንቺ ምን አስጨንቆሽ ነው ደውል የምትይኝ» አላት፡፡

«አየህ እሳቱን እዚያ እያለ ካላስቆምነው እዚህም ይመጣል፡፡ የአንዱ መቃጠል የሁላችንም መቃጠል ሆኖ ካልተሰማን በኋላ መከራው ለሁላችንም ይተርፋል» ትለዋለች፡፡ ሰውዬውም «አንቺ ያለሺው ውኃ ውስጥ እንዴት እሳቱ ያገኝሻል?» አላት፡፡ «እነዚያ ሰዎችኮ እሳቱ ከባሰባቸው ውኃ ለመቅዳት ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ እኔንም አብረው ሊወስዱኝ ይችላሉ፡» ስትል ትመልስለታለች፡፡

«ቀልደኛ ነሺ»ብሎ ትቷት ይሄዳል፡፡

«ከዕንቁራሪቷ እንደተለየ ሰውዬው መንገዱን ይዞ ጫካ ውስጥ ይገባል፡፡ ለካስ የቤቱ እሳት በርትቶ ጫካውንም ይዞት ኖሯል፡፡ መሐል ጫካ ከደረሰ በኋላ እሳቱ ይከብበዋል፡፡ ያን ጊዜ ዕንቁራሪቷ ያለቺው ትዝ አለው፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ምንም ሊያደርግ በማይችልበት ጊዜ ነው ትዝ ያለው፡፡

«እኛኮ ለእነዚያ አራዊት ጥብቅና መቆም ነበረብን፡፡ ምንም እንኳን ሽታቸውን ባንወደው፣ ምን እንኳን አንዳንድ ችግር ቢኖርባቸው፡፡ ምንም እንኳን በኛ ላይ ወጥተው ቢራኮቱ ግን ደግሞ ያስፈልጉን ነበር፡፡ ከኛ የተለየው ሁሉ የኛ ጠላት አይደለምኮ፡፡ ችግር ያለበት ሁሉ የማያስፈልግ አይደለምኮ፡፡ እኛ ለእነርሱ ጥብቅና የምንቆመው ለእነርሱ ብቻ ብለን አይደለም፡፡ ለራሳችን ነው፡፡ አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል አሉ ሰዎች፡፡»

«ይኼ ታሪክ አንድ ነገር ትዝ አስባለኝ አለ ዋርካ፡፡ አንድ ጊዜ ሁለት አዳኞች እኔ ሥር ቁጭ ብለው ሲያወሩ የሰማሁት ነው፡፡ በአንድ ወረዳ አንድ ፍርድ ቤት ነበር አሉ፡፡ ታድያ ዳኛው ሥራ የማይወዱ ስልቹ ነበሩ፡፡ ሰዎች ወደ እርሳቸው ጋ እንዳይመጡ የማያደርጉት ጥረት አልነበረም፡፡ የሉም፣ ታመዋል፣ መንገድ ሄደዋል፣ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ ንጉሡ ጠርቷቸው ሄደዋል፣ ሱባኤ ይዘዋል እያስባሉ ሰውን ሁሉ አስመረሩት፡፡

በዚህ ምክንያት ሰው እየተማረረ ወደ እርሳቸው አይመጣም ነበር፡፡ እርሳቸውም ቀኑን ሙሉ ሲበሉ፣ ሲጠጡ እና ሲተኙ ይውሉ ነበር፡፡ እንዲህ አድርገው ለብዙ ዘመናት እንደ ቆዩ ንጉሡ ገንዘብ ያንሳቸዋል፡፡ እናም የዳኞችን ቁጥር ለመቀነስ ይፈለጋሉ፡፡ አማካሪዎቻቸውን በየዳኞቹ ዘንድ ያለውን ባለ ጉዳይ ቆጥረው እንዲነግሯቸው ላኩ፡፡ የእኒያ ዳኛ ወንበር ሲታይ አንድም ሰው በአካባቢው የለም፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ሲጠየቁ እርሳቸውን ስለማያገኟቸው ወደ ጎረቤት ዳኞች እንደሚሄዱ ተናገሩ፡፡ እናም እኒህ ዳኛ ከሥልጣን ወርደው የንጉሡ አልጋ አንጣፊ ሆኑ፡፡ ባለጉዳዮቻቸው ለመኖር አስፈላጊዎቻቸው እንጂ ችግሮቻቸው አለመሆናቸውን የተረዱት አልጋ ሲያነጥፉ ነው»

«የኛ ነገር ደርሶባቸዋላ» አለ ዝግባው፡፡

እናም ሁሉም ጸጥ አሉ፡፡ የሚሰማው ድምፅ ዛፍ ቆራጮቹ ዝግባውን በመጥረቢያ ሲመቱ የሚወጣው ድምፅ ብቻ ነበር፡፡

ሳንሆዜ፣ ካሊፎርንያ

About The Author

Related Posts

Leave a Reply

Your email address will not be published.