ሰሞኑን በኢራን ከተሞች በመካሄድ ላይ ያሉት የተቃውሞ ሰልፎች ምክንያታቸው ለረጅም ዓመታት ሲብላሉ የቆዩ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደሆኑ የፖለቲካ ተንታኞች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ለብዙ ዓመታት ስር ሰድደው የቆዩ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ከኑሮ ውድነት መናር ጋር ተደምረው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን አገሪቱን ከ30 ዓመታት በላይ የመራውን መንግሥት ለመቃወም አደባባይ እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ይነገራል፡፡

የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በአብዛኛው በነዳጅ ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነና አገሪቱን በተከታታይ ያስተዳደሩት መንግሥታትም በዚያች አገር ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተንሰራፍተው የሚስተዋሉትን መዋቅራዊ ችግሮች ማስተካከል እንዳልቻሉ የኢራንን ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡

ከችግሮቹ መካከልም የውጭ ኢንቨስትመንት እጥረትና የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቅጥ ያጣ ጣልቃ ገብነትና አድራጊ ፈጣሪነት ዋነኛ ተጠቃሽ እንደሆኑ ይገለፃል፡፡ የአገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 9.6 በመቶ፣ የስራ አጥነቱ ደግሞ 13 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች መረጃዎች እንደሚሉት ደግሞ ዋጋ ግሽበቱና የሥራ አጥነቱ ቁጥር ከላይ ከተጠቀሱት እጥፍ ይሆናል፡፡

የሶደሬኦንድማንድን አፕልኬሽን በማውረድ ፊልሞች ከመለቀቃቸው በፊት ተመልከቱ Download SodereOnDemand app watch full movies before they are released. Apple, Android and Roku SodereOnDemand apps. 

          

እ.አ.አ ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 በሀገሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛውን ስፍራ በያዘችው ማሻድ ከተማ በመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰልፈኞች ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ፡፡ ተቃውሞው አድማሱን እያሰፋ ሲሄድ ግን የሚሰሙት ድምፆችም ይዘታቸውን እቀየሩ መጡ፤ በመንግሥት ላይ እንዲሁም በሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒ ላይ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች መስተጋባት ጀመሩ፡፡

ከተቃውሞ ሰልፈኞቹ መካከል ብዙዎቹ ወጣቶች እንደሆኑ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ እስካሁን በቁጥጥር ስር ከዋሉት የተቃውሞ ሰልፈኞች መካከልም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው ተቃውሞ ለሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ እስካሁን ድረስም ከ20 በላይ ሰዎች እንደሞቱና ከ500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንደታሰሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒ አስተዳደር የተነደፉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለተቃውሞው መነሻ እንደሆኑ ሲገልፁ፣ ሌሎች ደግሞ ሕዝቡ በሀገሪቱ መንግሥትና በመንፈሳዊ መሪው ክፉኛ እንደተማረረ ያብራራሉ፡፡ መጂድ ነመሃመድ የተባሉ ኢራናዊ ጸሐፊ በበኩላቸው ሙስና፣ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ እና ጥብቅ ሃይማኖታዊ አስተዳደር ለተቃውሞው መነሻ ምክንያቶች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በርካታ ኢራናውያን አገራቸው እ.አ.አ በ2015 ከዓለማችን ኃያላን አገራት ጋር ያደረገችው የኑክሌር ድርድር በአገሪቱ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ተነስተው የኢኮኖሚ መነቃቃት በመፍጠር በአገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ያረጋጋዋል የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ድርድሩ የታሰበውን ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፡፡

የአረብ ፖለቲካ ተንታኝና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማህጁብ ዝዌሪ፣ ‹‹የኢራን ሕዝብ ከኑክሌር ድርድሩ መልካም ውጤት ይገኛል ብሎ ተስፋ አድርጎ የነበረው ስሌት የተሳሳተ ነበር፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከያዙ በኋላ ሕዝቡ የፕሬዚዳንቱን ፖሊሲዎች ከግምት ውስጥ አላስገባቸውም፤ ሲጀመርም ድርድሩ ለኢራን ጠቃሚ አልነበረም›› ብለዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስምምነቱን ሊሰርዘው እንደሚችል በተደጋጋሚ መግለፁ የውጭ ባንኮች በአገሪቱ ለሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አበክረው ሲናገሯቸው ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ አገራቸው አሜሪካን ጨምሮ ኃያላኑ ከኢራን ጋር የተፈራረሙትን የኑክሌር ስምምነት እንደሚሽሩት ደጋግመው ማሳወቃቸው ነበር፡፡ ሰውየው እ.አ.አ በ2016 ፕሬዚዳንታዊ ስልጣኑን ከያዙ በኋላም ስምምነቱ አደጋ ውስጥ ገባ፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር የአገሪቱን የኑክሌር መርሃ ግብር በተመለከተ የቀረበላቸውን ስምምነት አልፈርምም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይባስ ብለውም አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት በቀሩት የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ጊዜያቸው እስካሁን ድረስ በኢራን ላይ ኢኮኖሚዋን የሚያሽመደምዱ ሁለት ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡

መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲ.ሲ ያደረገው የኢራናውያን-አሜሪካውያን ብሔራዊ ካውንስል መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ትሪታ ፓርሲ በበኩላቸው ኢራን በተለያዩ ጊዜያት የተጣሉባት ማዕቀቦች በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ ከሚስተዋለው ሙስና ጋር ተደምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እንደጎዱት ይገልጻሉ፡፡

‹‹በተለያዩ ጊዜያት በኢራን ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ አሽመድምደውታል፤ የኑክሌር ስምምነቱን እንደሚሽረው በሚዝተው የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ምክንያት ስምምነቱ የኢኮኖሚ ቀውሱን ከማረጋጋትና ከማሻሻል ይልቅ አባብሶታል›› ይላሉ፡፡

ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የኑክሌር ስምምነቱን አደጋ ላይ መጣሉ ለተቃውሞው መነሳት ብቸኛው መንስዔ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም ተብሏል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ስራ አጥነት፣ የዋጋ ንረትና የውጭ ኢንቨስትመንት እጥረት ለተቃውሞው ተጨማሪ ምክንያቶች ተደርገው ተጠቅሰዋል፡፡ ሀገሪቱ በምትከተላቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምክንያት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ ደግሞ በምጣኔ ሀብታቸው ከፈረጠሙት ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሀገራት ለመገለል ተገድዳለች፡፡

ፕሮፌሰር ማህጁብ ዝዌሪ እንደሚሉት፣ በዚያች አገር ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተንሰራፍተው የሚስተዋሉትና ሀገሪቱን ባስተዳደሩት መንግሥታት ሊቀረፉ ያልቻሉት መዋቅራዊ ችግሮች በተለይ የሕግ አውጭውንና የፋይናንሱን ዘርፍ ቀፍድደው ስለያዙት አገሪቱ ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ዝግ እንድትሆንና የከባድ ሙስና መነኻሪያ ለመሆን ተገድዳለች፡፡

እስላማዊው አስተዳደር ስልጣን ከያዘ ወዲህ መዋቅራዊ ችግሮቹ ስር መስደዳቸውንና መንግሥትም በየጊዜው ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ሲገጥመው በዜጎች ላይ ታክስ እየጨመረ የምጣኔ ሀብት ቀውሱን እንዳባባሰው ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ወር የአገሪቱ ፓርላማ በነዳጅ ላይ ሊደረግ የታሰበው የዋጋ ጭማሪ ላይ ውይይት መካሄዱ ይታወሳል፡፡

ኢራን በአካባቢው ፖለቲካ ውስጥ ያላት ተሳትፎም ለተቃውሞው መነሻ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰው በሶሪያ ፖለቲካ ውስጥ እጇን እንዳስገባች የምትታማው እስላማዊቷ ሪፐብሊክ፣ የፕሬዚዳንት በሺር አል-አሳድ አጋር እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ተቃውሞ ሰልፈኞቹም የኢራን መንግሥት በሺር አል-አሳድን ለመርዳት የሚያወጣው ገንዘብ አላስፈላጊ የሆነ ወጪ እንደሆነ ድምፃቸውን አስተጋብተዋል፡፡

የአረቢያ ፋውንዴሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ፊራስ ማቅሳድ፣ የአገሪቱ ዜጎች «ኢራን ከኑክሌር ስምምነቱ በኋላ ያገኘችው ገንዘብ የዋለው በኢራቅ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ ለሚገኙ ታጣቂዎች ነው» ብለው እንደሚያስቡ ገልፀዋል፡፡ ሰልፈኞቹ የአገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ መጠየቃቸው ከተቃውሞው ጀርባ ስር የሰደዱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች እንዳሉ ያመለክታሉ ብለዋል፡፡

‹‹በቀውስ የተናጠ ኢኮኖሚ ባለበት ሁኔታ ታክስ በመጨመር የሕዝብን ገንዘብ ለመዝረፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ የሕዝብን ቁጣ ከመቀስቀስ ያለፈ ፋይዳ የለውም›› ብለዋል፡፡

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚባለው ቡድን ቅጥ ያጣ ጣልቃ ገብነትና አድራጊ ፈጣሪነት ለፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ መሰናክል እንደሆነባቸው ይናገራል፡፡ ለዘብተኛ አቋም አላቸው የሚባሉት ፕሬዚዳንቱ ልዩ ልዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመወሰን ሲሞክሩ ከዚህ ቡድን የሚገጥማቸው ፈተና እጅግ ከባድ ነው ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንቱ ለውጥ የማምጣት እድላቸው የጠበበ ይሆናል፡፡

በቴህራን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት መሀመድ ማራንዲ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለበርካታ ዓመታት በዚህ ቡድን ሀገራዊ ኢንቨስትመንት ላይ የተንጠለጠሉ እንደሆኑና አገሪቱ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተጣሉባት ማዕቀቦች ምክንያት መንግሥት ዋና ዋና ፕሮጀክቶቹን ለዚሁ ቡድን እንዲያለማ ስለመስጠቱ ይናገራሉ፡፡

የአረብ ፖለቲካ ተንታኝና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማህጁብ ዝዌሪ እንደሚሉት ደግሞ፣ ኢራን የውጭ ኢንቨስተሮችን እንዳታገኝ መሰናክል የሆነው የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቡድኑ ነው፡፡ ቡድኑ ሀገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሏትን ሕጎች እንዳታፀድቅ በፓርላማው ላይ ጫና እንደሚያሳድር በመጠቆም፡፡ ለአብነት ያህል ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ሮሃኒ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያደረጉት ሙከራ ‹‹የምዕራባውያንን ባህል የሚያበረታታና ከእስላማዊ መርሆች ጋር ተፃራሪ›› ተብሎ በወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች እንደተጨናገፈባቸው ያስታውሳሉ፡፡

የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቡድኑ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነትና የብቻ ተጠቃሚነት ለተቃውሞው አንድ ምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችልም ያምናሉ፡፡

የኢራናውያን-አሜሪካውያን ብሔራዊ ካውንስል መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ትሪታ ፓርሲ በበኩላቸው፣ ‹‹አብዛኛው ኢራናውያን የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚባለው ቡድን ከሕግ በላይ የሆነ የሕገ-ወጦች ስብስብ እንዲሁም በአገሪቱ ለተንሰራፋው ሙስና ዋነኛው ተጠያቂ እንደሆነ ያምናሉ›› ብለዋል፡፡

አሁን አገሪቱን በመምራት ላይ ያለው የኢራን እስላማዊ መንግሥት እ.አ.አ በ1979 ስልጣን ከጨበጠ ወዲህ በውስጣዊና በውጫዊ ጉዳዮች (ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች) ላይ ሀይማኖት ተኮር አካሄድ መምረጡ ይገለፃል፡፡ ይህም የኢራን መንግሥት ለሽብርተኞች ይፋዊ ድጋፍ ያደርጋል በሚል ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እንዳቃቃረው ይነገራል፡፡

አንተነህ ቸሬ

About The Author

Related Posts

Leave a Reply

Your email address will not be published.